አንድ አድርገን ጥር 21 2007 ዓ.ም
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ከጥቂት ወራት በፊት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና በማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ላይ በተከታታይ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዘወርት”በሚል ዐቢይ ርዕስ ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ተከታትያለኹ። ዶ/ር መርሻ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም የክርስትና መድረክ የነበራትንና አሁንም ያላትን ልዩ ስፍራና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በተመለከተ ያቀረቡት ታሪክ የዳሰስ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ለዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ምክንያት ኾኖኛል።
ዶ/ር መርሻ የኢትዮጵያ ቤ/ን የክርስትና እምብርት ከሆነችው ከእስራኤል ጋር ከዘመነ አበውና ከሕገ ኦሪት ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ ስለነበራት ሦስት ሺህ ዘመናትን ስላስቆጠረው ረጅም ታሪኳ፣ ክርስትያናዊ ጉዞዋና ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን አጠር ባለ መልኩ ለመግለጽ ሞክረዋል። ዲያቆን መርሻ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸውም የኢትዮጵያ ቤ/ን በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአሜሪካና በካረቢያን ለረጅም ዓመታት የቆየውን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ተንትነዋል።