Wednesday, February 20, 2013

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን አንቋሸዋል የተባሉ በእስር ተቀጡ

  •  ፍርድ ቤቱ ለእያንዳንዳቸው 6 ወር ፈርዶባቸዋል፡፡
  •  መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ጀርባ የመሸጉት ቡድኖችን ይወቋቸው፡፡
(አንድ አድርገን የካቲት 13 2004 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን የሚያንቋሽሽና የሚያስተሃቅር ወንጀል ፈጽመዋል ወይም የወንጀል መቅጫ ህጉ ቁጥር 32/1ሀ ና 492/ሀ ላይ የተመለከተውን የህግ ድንጋጌ ተላልፈዋል የተባሉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ፡፡
ዐቃቢ ሕግ በመሰረተው ክስ ዲያቆን ሀብቴ ተፈራ እና ዲያቆን ጓዴ ሳህሉ የሚል የመታወቂያ ስም ያላቸው ተከሳሾች የኦርቶዶክስ ተዋህዶን ሃይማኖት የሚያቃልል ጽሁፍ የያዘ ፓምፕሌት ይዘው ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ደብረ ታቦት ከተማ በመሄድ ባሰራጩት ጽሁፍ “እንደ እንቧይ ካብ  በገዛ ራሱ  የፈራረሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተሰኝው እምነት ከንቱ መዋቅር ነው ፤ እሁድ እንደ ማንኛውም የስራ ቀን ነው ፤ ቤተክርስቲያንን የሚመሩ ጳጳሳት ዝሙታን ናቸው…” የሚሉ እና የመሳሰሉት ጽሁፎች በየቦታው ሲበትኑ እንደነበርና ይህም በሰውና በሰነድ ማስረጃ ከበቂ በላይ ተረጋግጧ ተብሏል፡፡

አቡነ ሳሙኤል የምረጡኝ ዘመቻ ጀመሩ


በሳምንት ከ20 ሺህ በላይ በመታተም ለንባብ የሚበቃው ሰንደቅ ጋዜጣ የካቲት 13 2005 ዓ.ም በፊት ገጽ ይዞት የወጣው ዜና
  • 500 ሺህ ብር በአበል መልክ እንዲከፈል አድርገዋል
(አንድ አድርገን የካቲት 13 2005 ዓ.ም)፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት  የተለዩት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን የሚተካ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለማስመረጥ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ ከዚህ የፓትርያርክ ምርጫ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያኒቷ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በነበሩት ወቅት ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው የነበሩት አቡነ ሳሙኤል  በቀጣዩ ምርጫ ስድስተኛው ፓትርያርክ ሆነው እንዲመረጡ ብጹአን ሊቃነ ጳጳሳትን ፤ የቤተክህነት አስመራጮችን ፤ የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ስራ አስኪያጆችንና ታዋቂ ግለሰቦችን በማግባባት ላይ መሆናቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ለጉዳዩ በጣም ቅርበት ያላቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡

Tuesday, February 19, 2013

የአቶ መለስ ዜናዊ ሃውልት ሲመረቅ አቡነ ጳውሎስ ያረፉበት ቦታ እንደታጠረ ነው



(አንድ አድርገን የካቲት 12 ፤ 2005 ዓ.ም)፡- የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር የአቶ መለስ ዜና ሀውልት ትላንትና የካቲት 11 2005 ዓ.ም ቤተሰቦቻቸው እና ጥቂት ባለስልጣኖች በተገኙበት ተመረቀ ፡፡ የዲዛይንና የኤሌክትሪካል ስራውን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ ስራው የመከላከያና ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ድርጅት አማካኝነት የተሰራ ሲሆን ስራውን  ለማጠናቀቅ ከስድስት ወር በላይ መፍጀቱ ታውቋል፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ አስከሬን ያረፈበት ቦታ በመንበረ ጸባኦት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል ግቢ ውስጥ በስተግራ በኩል  በግምት ከ260 እስከ 300 ካሬ ቦታ የፈጀ ሲሆን አስከሬኑ ያረፈበት ቦታ ከ40 ካሬ እንደማይበልጥ በቦታው ተገኝተን ለማወቅ ችለናል፡፡ ይህ ሃውልት ሙሉ በሙሉ በጥቁር እምነበረድ የተሰራ ሲሆን በምሽት የተለየ ውበት የሚሰጡት በርካታ መብራቶች ተገጥመውለታል ፡፡  ሃውልቱ ላይ “የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ከ1947-2004 ዓ.ም” የሚል ጽሁፍ ብቻ በአማርኛ እና በእግሊዝኛ ተጽፎበታል፡፡ ሃውልቱ ላይ ፎቶም ሆነ ሌላ ጽሁፍ አይታይበትም፡፡ ቦታው ተገኝተን እንደጎበኝነው ሃውልቱ ለህዝብ እይታ ክፍት የሆነ ሲሆን ቦታው ላይ ባሉት በአራት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጥበቃ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ በግቢ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሃውልቶች ፊታቸው ወደ ቤተክርስቲያኑ ያዙሩ ሲሆን የአቶ መለስ ሃውልቱ ግን  ፊቱን ወደ ውጭ በር አድርገው ሰርተውታል፡፡ ከወራት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዝግ ስብሰባ  “መለስ ፋውንዴሽን” የሚል ተቋም መንግሥት ያቋቋመ ሲሆን ፤ ፋውንዴሽኑ ስራውን ሲጀምር አስከሬኑን ከቅድስት ሥላሴ በማንሳት አስገነባዋለሁ ወደሚለው ህንጻ እንደሚያዛውር ለማወቅ ተችሏል፡፡

Monday, February 18, 2013

“ምርጫ ውስጥ ስካተት አትርሱኝ” አቡነ ጎርጎርዮስ

(አንድ አድርገን ህዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም)፡-የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፤ ክብር ፤ ባህል ፤ እምነት ፤ሥርዓት ፤ መንግሥትና ቋንቋ ያቋቋመች ፤ የማትናወጥ ከመሆኗ ጋር ፤ ከሔኖክ ፤ ከመልከ ጼዲቅ ፤ ከነቢያትና ከሐዋርያት የተላለፈውን ትምህርት ፤ ሥርዓት ፤ እምነት ከትውልድ ወደ ትውልድ ስታስተላልፍ የኖረች ፤ በማስተላለፍ ላይ ያለች ፍኖተ ሕይወት ናት፡፡ ቅዱሳን አበውን ፤ ኃያላን ነገሥታትን ፤ ልዑላን መሳፍንትን ፤ ክቡራን መኳንንትን ፤ ዐይናሞች ሊቃውንትን በሥጋ ፤ በነፍስ ወልዳ ያሳደገች የሌላ የማትፈልግ ፤ የራሷንም የማትለቅ ዕጥፍ እናት ፤ ስንዱ እመቤት ናት፡፡” በማለት ስለ ቤተክርስቲያን የተናገሩት ታላቁ ሊቅ የቀለም ቀንድ አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ ፡፡ እንዲህ የተባለላት ቤተክርስቲያን  ዛሬ ከእርቀ ሰላም የተከደነ አጀንዳ በኋላ ስድስተኛ ብላ ፓትርያርክ ለመሾም ወሳኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ 

ብጹአን አባቶቻችንን እወቋቸው


PART - 1
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት አድርጋ የሾመቻቸው በሕይወት ያሉና በሕይወት ያለፉ አባቶች ጥቂቶቹ………..


“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።ከሄድሁ በኋላ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኞች ተኩላዎች እንዲገቡባችሁ፥ ደቀ መዛሙርትንም ወደ ኋላቸው ይስቡ ዘንድ ጠማማ ነገርን የሚናገሩ ሰዎች በመካከላችሁ እንዲነሡ እኔ አውቃለሁ።

 የሐዋርያት ሥራ 20 ፤ 28-30 



Sunday, February 17, 2013

ከጋዜጦች




ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት ዕጩዎች ዛሬ ይለያሉ
 
(አዲስ አድማስ ቅዳሜ የካቲት 9 2005 ዓ.ም)፡- ፡- የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ፤ ካህናትና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ እንዲጠቁሙ ያወጣው የስምንት ቀን መርሐ ግብር አርብ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የተጠናቀቀ ሲሆን ለፓትርያሪክነት የተጠቆሙት ዕጩዎች ቅዳሜ ይለያሉ፡ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን ቅን መሪ እንዲሰጥ፣ የወደደውንና የፈቀደውን በመንበረ ፕትርክናው እንዲያስቀምጥ ካህናትና ምእመናን አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ የታዘዘው የአንድ ሳምንት የጸሎት ሱባኤ እስከ ምርጫው ፍፃሜ የካቲት 21 ቀን 2005 ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት ተላልፏል፡፡ ዐዋጅም መፈጸሙ ተነግሯል፡፡ በምርጫው መሪ ዕቅድ መሠረት፣ የካቲት 9 ቀን  ካህናትና ምእመናን የዕጩ ፓትርያሪክ ጥቆማ የሰጡበትን ቅጽ የያዘው የታሸገ ሣጥን ተከፍቶ ተጠቋሚዎቹን የመለየት ሥራ እንደሚሠራ የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

Wednesday, February 13, 2013

የፕትርክናው ምርጫ አንዳንድ ሰበዞች




ከአጥናፉ አለማየሁ
(አንድ አድርገን የካቲት 6 2005 ዓ.ም)፡- አንድ ፓትርያርክ ከስልጣን ቢወርድ ወይም በስጋ ዕረፍት ቢለይ በ1991 የወጣውና በሥራ ላይ የሚገኝው ሕገ ቤተክርስቲያን የሚከተለውን ይላል

ስለ ቅዱስ ፓትርያርክ ምርጫ

1.  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የቤተክረስቲያኒቱ ሕግና ቀኖና በሚፈቅደው መሠረት ተመርጦ ይሾማል፡፡
2.  ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ፓትያርክ ምርጫ የሚወሰነው ቁጥር መሠረት አስመራጭ ኮሚቴ ይቋቋማል፡፡
3.    ለፓትርያርክነት የሚመረጡ እጩዎች ለሊቃነ ጳጳሳት ፤ ከጳጳሳት ከኤጲስ ቆጶሳት መካከል ሲሆን ብዛታቸው ከሶስት ያላነሰ ከአምስት ያልበለጡ ይሆናሉ፡፡
4.    አስመራጭ ኮሚቴው ዕጩዎቹን ጠቁሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀርባል፡፡ በቤተክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ምርጫው እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡
5.  መራጮች የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተክህነት ጠቅላይ ስራ አስኪያጅ የመምሪያና የድርጅት ሃላፊዎች ፤ የጥንታውያን ገዳማት አበምኔቶች  ፤ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ከየአህጉረ ስብከቱ ሰበካ ጉባኤያት በእድሜ ከ40 ዓመት ያላነሱ የካህናትና የምዕመናን ተወካዮች ፤ እንዲሁም እድሜያቸው ከ22 እስከ 40 ዓመት የሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች ሲሆኑ ፤ በጠቅላላው በሰበካ ጉባኤ የሚወከሉ ከአንድ ሀገረ ስብከት 12 ሆነው በሥጋወ ደሙ የተወሰኑ ፤ በሕገ ቤተክርስቲያን የጸኑ መሆን አለባቸው፡፡
6.    የምርጫ አፈጻጸም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ይሆናል፡፡
7.    የተመረጠው ፓትርያርክ የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ቀኖናውን ሊጠብቅና አድልዎ በሌለው መልኩ ቤተክርስቲያኒቱን ሊያስተዳድር ቃለ መሐላ ይፈጽማል፡፡
8.  ከዚህ በላይ የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ ስለ ፓትርያርክ ምርጫ ቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ያወጣል፡፡

እንግዲህ ከአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ ስድስተኛውን የቤተክርስቲያኗን ፓትርያርክ ለመሰየም ከዚህ በኃላ የሁለት ሳምንታት እድሜ ብቻ ይቀራል፡፡  አስመራጭ ኮሚቴው ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ “ሀይሁብ መርሐ ርቱዕ ለቤተክርስቲያን” ማለትም ለቤተክርስቲያን ቅን መሪ የሚሰጥ እግዚአብሔር የወደደውንና የፈቀደውን ያስቀምጥ ዘንድ ከየካቲት አንድ እስከ ስምንት  የአንድ ሱባኤ ጸሎት ምህላ ካወጀ ዛሬ ስድስተኛውን ቀን ይዟል፡፡

Monday, February 11, 2013

ካህናትና ምእመናን ዕጩ ፓትርያሪክ እንዲጠቁሙ ተጠየቀ


  • ከመንግሥት የተወከሉ ሶስት ሰዎች ምርጫውን ይታዘባሉ፡፡  (በፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ)
(አዲስ አድማስ ፡-)  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ÷ ካህናት እና ምእመናን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባት ሊኾን ይገባል የሚሉትን ዕጩ በመጠቆም እንዲሳተፉ ጠየቀ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው፣ ስለ ስድስተኛው ፓትርያሪክ የምርጫ ሂደትና የተመረጡት ፓትርያሪክ ስለሚሾሙበት ቀን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ካህናትና ምእመናን ግልጽ ለማድረግ ከትላንት በስቲያ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ ባስተላለፈው ጥሪ÷ በሀገር ውስጥ ያሉ ካህናት÷ አገልጋዮች መኾናቸውን፣ ምእመናንና የሰንበት /ቤት ወጣቶች ደግሞ የአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን አባላት መኾናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመያዝ በአስመራጭ ኮሚቴው /ቤት በአካል በመቅረብ፣ ከሀገር ውጭ የሚገኙትም በፋክስ ቁጥር 011 - 1567711 እና 011-1580540 ከየካቲት 1 - 8 ቀን 2005 . ድረስ ዕጩአቸውን እንዲጠቁሙ ጠይቋል፡፡

Sunday, February 10, 2013

ለስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ 800 መራጮች ድምፅ ይሰጣሉ


-    ምርጫው  የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ይፈጸማል 
( Reporter:-  )የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስድስተኛው ፓትርያርክ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደምትመርጥና 800 መራጮች ድምፅ እንደሚሰጡ አስታወቀች፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የካቲት 21 ቀን ለሚፈጸመው የፓትርያርክ ምርጫ የሚቀርቡት አምስት ዕጩ ፓትርያርኮች የካቲት 18 ቀን ለሕዝብ ይፋ ይሆናሉ፡፡

ስድስተኛውን ፓትርያርክ የሚመርጡት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምርያ ኃላፊዎች፣ ጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፣ ካህናት፣ ምዕመናን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መሆናቸውና ቁጥራቸውም 800 መሆኑን ሰብሳቢው አስረድተዋል፡፡

Tuesday, February 5, 2013

ልዩ ልዩ


ስም ማጥፋት

(ጥር 28 2008 ዓ.ም)፡- ዛሬ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ማታ ከሁለት ሰዓቱ ዜና በኋላ ሽብርተኝነትንና ሃይማኖትን በተመለከተ አወዛጋቢ ፊልም ያቀርባል ፤ የፊልሙ ማጠንጠኛ “ኢስላማዊ መንግስት” ለመመስረት እቅድ ነበረን የሚሉትን ሰዎች በዶክመንተሪ መልክ ለህዝብ ማቅረብ ነው ፤ ይሄ ፊልም በቴሌቪዥን እንዳይተላለፍ በሽብርተኝነት የተከሰሱት ሰዎች ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ዛሬ የይታገድልን ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል ፤ ጥያቄያቸውም መልስ እንደማያገኝ ይገመታል ፤ትላንት ማታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ሽብርተኝነትና አደጋውን በሚመለከት ቃለ መጠይቅ ባደረገላቸው ወቅት “አንዳንድ ክርስትያኖችና ሙስሊሞች” እያሉ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተስተውሏል ፤ በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ የሙስሊም ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ሰዎች በቃሊቲ እንዳሉ ይታወቃል ፤ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ አሸባሪ ወይም አክራሪ ተብሎ የታሰረ አንድም ክርስትያን ወይም የክርስቲያን ተቋም በሌለበት ሁኔታ “አንዳንድ ክርስትያኖች” በማለት የሚሰጥ አስተያየት ተገቢ ነው ብለን አናስብም ፤ “ሊበሏት ያሰቧትን …” በሚያስብል መልኩ በሆነውም ባልሆነውም ቦታ ስም መጥራት ከስም ማጥፋት አይተናነስም ፤ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናው በመጨረሻ የፓርላማ ንግግራቸው “ይህ የአክራሪነት አመለካከት አፈር መልበስ አለበት” ብለው ነበር ፤ አፈር መልበስም ካለበት በዚህ ጎራ የቆሙትንና ያልቆሙትን ሰዎች መለየት የመጀመሪያ ስራ መሆን ሲገባው ሰው ሃይማኖቱን ስለጠበቀ እና በአግባቡ ስለተከተለ ያልሆነ ስም መስጠት ተገቢ ብለን አናምንም